
ማስታወቂያ እና ዜና
“የሁለት አለም ሰው” መጽሐፍን በተመለከተ ከደራሲዋ የተሰጠ
መግለጫ
ስለ እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ የህይወት ታሪክ የተጻፈው መጽሐፍ ያለ ፈቃዳቸውና ያለ እውቅናቸው የታተመ መሆኑን በመግለጽ በፌይስ ቡክ ላይ ለተለቀቀው ውንጀላ ከደራሲዋ የተሰጠ መግለጫ።
ከአስር አመት በላይ እየሩሳሌም ከተማ ስኖር እሳቸውን አግኝቼ ባነጋግራቸው ብዬ ያልተመኘሁበት ቀን አልነበረም። እማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ የአገር ቅርስ በመሆናቸው እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አከብራቸዋለሁ። ለእማሆይና ለቀሪው ቤተሰብ ምሳሌ የሆኑትን አባታቸውን ከንቲባ ገብሩ ደስታን ደግሞ በበለጠ አደንቃቸዋለሁ።በ 1860ዎቹ ዓ ም ከጐንደርና ከትግራይ አካባቢ ወደ እየሩሳሌምና ወደ ባዝል (ስዊዝ) በሚሲዎናውያን ተወስደው በመንፈሳዊ ኮሌጅ ከተማሩት ኢትዮጵያውያን መካከል አገራቸው ተመልሰው በተለያዩ የሥራ ሃላፊነት የሠሩና የጐላ ሥም ተክለው ያለፉ ሰው በመሆናቸው ነው የማደንቃቸው።
እንግዲህ የኒህ ሰው ልጅ ዘመናዊ የሙዚቃ ትምህርት ተምረው በተለያየ የሥራ መስክ ተሳትፈው በሃያ አምስት አመት ዕድሜያቸው ድንገት ገዳም ገብተው መነኮሱ። ለምን? የሚለው ጥያቄ ነበር የበለጠ ወደ እማሆይ እንድቀርብ የገፋፋኝ። ስለሆነም ሊያስተዋውቁኝ ፈቃደኛ ከሆኑ ሰው ጋር በመሄድ ተዋወቅን ።የህይወት ታሪካቸውን ለመጻፍ እንደምፈልግና ፈቃደኛ ይሆኑ እንደሆን ጠየቅኋቸው ።በደስታ ጥያቄዬን ተቀበሉት።በዚህ ተስማምተን በየሳምንቱ እቤታቸው በመሄድ ያለፈ ታሪካቸውን ያጫውቱኝ ጀመር። ለማጣቀሻ እንዲሆነኝ ወንድማቸው ኮሎኔል ዳዊት ገብሩ የጻፉትን
1ኛ/ “ከንቲባ ገብሩ ደስታ የኢትዮጵያ ቅርስ” የሚል መጽሐፍ
2ኛ/ የተለያዩ ራሳቸው በእጅ የጻፉዋቸው ግጥሞች በኋላ በኮምፒውተር የተገለበጡ
3ኛ/ በዛ ያሉ የራሳቸውና የቤተሰብ ፎቶግራፎች
4ኛ/ ከወ/ሮ ማርታ ነሲቡ በኮምፒውተር የተጻፈ ደብዳቤ
5ኛ/ለገዳሙ የገቢ ማስገኛ እንዲሆን ያሳተሙት በራሳቸው የተጻፈ “The Beautiful Land Of The Queen Of Sheba Ethiopia”የሚል ባለ አራት ገጽ ጥራዝ ሰጥተውኝ በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቃሎ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በመሄድ በግሌ በአዲስ አበባ በኖሩበት ሠፈር ጐንደር እማሆይ በቆዩባቸው አመታት በጊዜው በቤተመንግስት ዙሪያ የነበሩ አዛውንቶችን በማነጋገርና በርከት ያሉ መጻህፍትን በማንበብ መረጃዎችን ሰብስቤያለሁ።ከዚህ በተጨማሪ
1ኛ/ ከልጅነት ጀምሮ ከሚያውቋቸው በኋላም ጐንደር በ 1950ዎቹ በቆዩበት ወቅት ይቀርቧቸው ለነበሩት ጓደኛቸው ለክብርት ወ/ሮ ማርታ እምሩ (የልዑል ራስ እምሩ ልጅ ) ደብዳቤ እንድሰጥ ፦ ፎቶግራፍ አንስቼ እንድመጣና መጽሐፉ ውስጥ እንዳካትተው
2ኛ/ በእሳቸው የህይወት ታሪክ ዙሪያ ዶኩመንታሪ ፊልም ለመስራት አስበው ከነበሩት ከወ/ሮ ጀማነሽ ሰሎሞንና ከአቶ ዮናስ ጐርፌ እጅ የሚገኙትን ጠቃሚ መረጃዎች እንድቀበል ደብዳቤ ሰጥተውኝ የነበረ ቢሆንም
ሀ) ወ/ሮ ጀማነሽን በአካል ማግኘት አልቻልኩም። ከዚህም በላይ መረጃዎቹንም ለራሳቸው ለእማሆይ እንጂ ለሌላ ሰው እንደማይሰጡ በእማሆይ የእህት ልጅ በወይዘሪት ጃፒ ይልማ አማካኝነት ተነገረኝ።
ለ) አቶ ዮናስ ጐርፌ በጃቸው የነበረውን መረጃና በፕሮጀክተሮች ሊታዩ የሚችሉ ፊልሞችን የሰጡኝ ከመሆኑም በላይ ወ/ት ጃፒ ይልማ የተለያዩ ጽሁፎችን የእናቷን የወ/ሮ ገነት ገብሩን የአያቷን የእማሆይ ካሳዬ የሌምቱን የአርባ ቀን መታሰቢያ መጽሔቶች እንዲሁም የጀነራል ከበደ ገብሬን የህይወት ታሪክ የሚገልጽ ማስታወሻ ሰጥታኝ አስፈላጊ የሆኑት ተመርጠው በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን በእጄ የነበሩትን መረጃዎች በሙሉ መልሸላቸዋለሁ።
3ኛ/ ተጨማሪ የቆዩ የቤተሰብ በተለይም የእህትማማቾቹን ፎቶግራፎች ከአቶ ዳንኤል አሰፋ እንድቀበል በጠቆሙኝ መሰረት በኢሜል ልከውልኝ በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቃሏል።
በዚህ ሁኔታ ማጣቀሻ ጽሁፎችን አሟልቶ ተጽፎ የመጽሐፍ ስም እንዲመርጡ ሶስት ምርጫ ተሰጥቷቸው መርጠው መጽሐፉ ታተመ። ለናሙና የታተመውን አንድ መጽሀፍ አይተው ደስ ብሏቸው ህትመቱ እንዲቀጥል ተስማሙ።መጽሐፉ ታትሞ ካበቃ በኋላ በገዳሙ ውስጥ ካሉት አባቶች መካከል አባ ገብረስላሴን ጠርተው መጽሐፉ እንዲመረቅ እዚሁ ገዳሙ ውስጥ ቦታ እንዲፈቀድ ምን እናድርግ ብለው እኔ በተገኘሁበት ጠየቁ።አባ ገብረስላሴ መጋቢውን ማነጋገር እንዳለብን አስረዱን ። እኔን (ደራሲዋን) መጋቢው አባ ገብረወልድ ከአቡነ ዳንኤል ጋር ካገናኙና ከአነጋገሩን በኋላ ደብረገነት ኪዳነምህረት ገዳም ውስጥ ባለው አዳራሽ እንዳስመርቅ ፈቃድ ተሰጠኝ።
በዚህ መሰረት ለመነኮሳት ተነግሮ መዘምራንና ጥሪ የተደረገላቸው ሰዎች በተገኙበት እሁድ ፌብሯሪ 9/2014(የካቲት ሁለት እንደ ኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር) ሊመረቅ አርብ ፌብሯሪ 7/2014 ማታ ደውለው በመጽሐፉ ስም አስተያየት ሰጥተውኝ ቅር ብሎኛል እንዲቀየር እፈልጋለሁ ከመጻህፉ ውስጥ ደግሞ ተቀደው እንዲወጡ የምፈልጋቸው ገጾች ስላሉ እንዳይመረቅ አሉኝ። እኔም ሃሳባቸውን ይቀይራሉ ብዬ በማሰብ ቀኑን ሰረዝኩት።ማማከርና አስተያየት መቀበል ከፈለጉ ለናሙና በወጣበት ወቅት ነበር እንጂ ታትሞ ከወጣ በኋላ አልነበረም። በኔ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ኪሳራ እንኳን ግምት ውስጥ ማስገባት አልፈለጉም። በሃሳባቸው ስለጸኑ መጽሃፉ ሳይመረቅ ለሽያጭ ቀረበ።
ነገሮች በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ህገ ወጥ ሥራ የሰራሁ በማስመሰል በእኔ ላይ የሚደረግ ስድብና የስም ማጥፋት ዘመቻ እኔን ሳይሆን እማሆይን ትዝብት ላይ ለመጣል የፈለጉ ሰዎች ሤራ መሆኑን ያረጋግጣል። እማሆይ እንዲህ አይነት ውንጀላ ውስጥ ይገባሉ ብዬ ለማለት ያስቸግረኛል። ታሪካቸውን የሚያጐድፍ ምን ነገር ተጻፈባቸው? ተቀደው እንዲወጡ የተፈለጓቸው ገጾች ደግሞ ለተጠየቁት ጥያቄ ማስተባበያ የሰጡበት ስለሆነ ቅሬታ የሚፈጥር አይደለም።
ይህ በእንዲህ እያለ ግራ ቀኛችን ሳያነጋግሩ ከንቱ ውንጀላን በቪዲዮ ቀርጸው በፌስ ቡክ የለቀቁት አቶ አሥራት በጋሻው የስም ማጥፋት ወንጀል ተባባሪ መሆናቸው የተቀናጀ ደባ እየተሰራብኝ መሆኑ አሳዝኖኛል። እንዲህ ያለ የስም ማጥፋት ድርጊት ደግሞ በህግ ከፍተኛ ወንጀል ነው። ያስቀጣል። ወደ ስም ማጥፋት ዘመቻ ከመሄድ ወደ ህግ ቦታ መሄዱ ተቀባይነት ይኖረው ነበር። እማሆይ በህግ ሊጠይቁኝ የሚችሉ ጉዳዩን ከመነሻው የሚያውቁ ህጋዊ ወኪል አሏቸው። በጣም የሚገርመው ደግሞ የሚተቹትና ነገር የሚያቀጣጥሉት መጽሃፉን ያላነበቡት ሰዎች መሆናቸውን ሳይ አላማቸው ምንድን ነው? እያነጣጠሩ ያሉት እኔ ላይ ወይስ እማሆይ ላይ??
በመጨረሻ ለእማሆይ እረጅም እድሜና ጤና እመኛለሁ።
ስዋሰው ብርሃኑ ደስታ
እየሩሳሌም
4 ኖቬምበር 2014
